ቀልጣፋና ፈጣን እንቅስቃሌ ለፈጣን ስኬት
(The Law of Inertia)
አይዛክ ኒውተን በመባል የሚጠራው ታዋቂ የስነ ፊዚክስ ምሁር ከደረሰባቸው ህጎች ውስጥ አንዱ ነው፤ የኒውተን የመጀመሪያ ህግ ወይም ደግሞ «Newton's first law of motion»። ይህ ህግ እንደሚለው ከሆነ የትኛውም በእንቅስቃሴ ውስጥ ያለ ነገር ውጫዊ ተፅዕኖ እስካላረፈበት ጊዜ ድረስ በእንቅስቃሴ ውስጥ ይቀጥላል፤ እንዲሁ ደግሞ የትኛውም የተቀመጠና የማይንቀሳቀስ ነገር አንዳች ውጫዊ ተፅዕኖ እስካሳረፈበት ጊዜ ድረስ ባለበት ተቀምጦ ይቀራል። በራሱ ቋንቋ እንዲህ ይገልፀዋል «A body in motion will remain in motion and a body at rest will remain at rest unless and otherwise an unbalanced external force is applied on it.» (This is Called Newton's first law of motion) ይህ ህግ በዩኒቨርሳችን ውስጥ ባሉ የትኛቸውም ቁስ አካላዊ ነገሮች ላይ የሚሰራ ህግ ነው። ነገሩ ልክ እንደ ጋዝ ሞለኪውል የማይታይ ወይም ደግሞ ልክ እንደ ዳይኖሰር ግዙፍ ሊሆን ይችላል፤ አልያም ደግሞ ልክ እንደ ቫይረስ እጅግ ደቃቅ አልያም ደግሞ ልክ እንደ ጁፒተር ፕላኔት ግዙፍ ሊሆን ይችላል። የትኛውም አይነት ነገር የዚህ ተፈጥሮ ህግ ይመለከተዋል። ይህን ህግ አይዛክ ኒውተን ሊያገኘው ቻለ እንጅ ይህ ዩኒቨርስ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የሚመራበት አንዱ የተፈጥሮ ህግ ነው።
እርግጥም ይህ ህግ የእያንዳንዳችንን ህይወት ይመለከታል። አንድ ግለሰብ አንድን ነገር አሳክቶ ማግኘት የሚችለው በእንቅስቃሴ ውስጥ ሲሆን ነው። እንቅስቃሴ በሌለበት ሁኔታ የሚመጣ ስኬት የለም። የአንድ ሰው ስኬታማነት ለስኬቱ በተንቀሳቀሰበት መጠን ውስጥ ይወሰናል። ዝቅተኛ እንቅስቃሴ ወይም ቅልጥፍና ያልተላበሰ አሰራር እየከወኑ የተሻለ ስኬት መጠበቅ አይቻልም። በመሆኑም ውጤታማ ሆኖ ለመገኘት ለውጤት የሚያበቃ ቀልጣፋና ከጊዜ አንፃር ሲለካ ፈጣን እንቅስቃሴን መተግበር ያስፈልጋል። አንድ ሰው መስነፍ ከጀመረ በኒውተን ህግ መሰረት ስንፍናው ተጠናክሮ ይቀጥላል። አንዳች ከስንፍናው የሚያባንነው ከባድ ችግር ወይም ዕዳ እስኪፈጠር ድረስ (an unbalanced external force)። እንዲሁም ደግሞ አንድ ሰው የስራ ትጋት ውስጥ መግባት ሲጀምር ይህ ትጋት የበለጠ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይችላል! ይህን የስራ ትጋት የሚያስቆም አንዳች ውጫዊ አደጋ ወይም ደግሞ የይበቃኛል እርካታ (An unbalanced internal force) ግለሰቡን ካላዘናጋ በስተቀር።
በመሆኑም በተቻለ መጠን ትጉና ጠንካራ የስኬት ሰዎች በመሆን ወደፊት ለመገስገስ እንደኒውተን ህግ አንፃር ሁልጊዜም በእንቅስቃሴ ውስጥ መሆን መቻል አሰብን። አንድ ቦታ ላይ ለሪጅም ጊዜ መቀመጥ የበለጠ የስንፍና ሀይልን (inertia) የሚጨምር ሲሆን ብዙ መተኛትም በተመሳሳይ መልኩ የስንፍናን ሀይል የሚጨምር ነው። ብዙ ማውራት፣ ብዙ መቀመጥ፣ ብዙ መተኛት የበለጠ የእንቅስቃሴ ሀይልን የሚገድብና ስንፍናን የሚያበረታታ ነው። በአንፃሩ ደግሞ ፈጣን አረማመድ፤ የጧት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ፤ የትኛውም ጉልበትን የሚጠይቅ እንቅስቃሴ የበለጠ የመነቃቃትንና በቀጣይም ለሌላ ፈጣን የአሰራር ቅልጥፍና የሚያበቃ ሀይልን ይፈጥራል። ፈረንጆች እንደሚሉት ነው «Motion induces emotion» ታዝበን ከሆነ ትንሽ ዳንስ ወይም ስፖርት በስራን ቁጥር በውስጣችን የበለጠ መነታቃት ይፈጠራል። ይህ ደግሞ የበለጠ የስራ መንፈስንና ቅልጥፍናንን ይፈጥራል።
በስነ አዕምሮ ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ አዕምሯችን በተቀመጠ ቁጥር ወይም ሰውነታችን በሰነፈና በዝግታ እንቅስቃሴ ውስጥ ባለ ቁጥር አዕምሯችን የበለጠ የሚያስበው ወደኋላ ነው ወይም ደግሞ ስላለፈ የአኗኗር ትዕይንት ነው። ይህ ደግሞ የሚጠቅም ልማድ አይደለም። ፈጠን ያለ የወደፊት እንቅስቃሌ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ደግሞ አዕምሯችን ስለ ወደፊቱ ግብና እቅድ የማስቡ እድል ከፍተኛ ነው። አዕምሯችንም ስለወደፊቱ ትኩረት ሰጥቶ ማሰብ ሲጀምር ደግሞ ስኬታችንም የበለጠ ይጨምራል ማለት ነው። በመሆኑም በተቻለ መጠን በእንቅስቃሴ ውስጥ ለመሆን ጣር። ፈጣን ኢረማመድ፣ ፈጣን አሰራር፣ ፈጣን ቀጠሮ፣ እጥር ምጥን ያለ ስብሰባ፣ እጥር ምጥን ያለ ወሬ፣ እጥር ምጥን ያለ እንቅልፍ፣ እጥር ምጠን ያለ የምሳ ፕሮግራም በማከናወን እንቅስቃሴህን በመጨመር ወደ ኋላ የሚጐትትህን ውስጣዊ የኢነርሺያ (Inertia) ሀይል ቀንሰው። እንዲህ ባደረክ ቁጥርም ውስጣዊ የመነቃቃት ሀይልህንና የበለጠ ቀልጣፋ የአሰራር ባህልን ለማዳበር በእጅጉ ያግዝሀል። ነገር ግን በተቃራኒው የሚሆን ከሆነ ደግሞ የኒውተን የመጀመሪያ ህግ በአንተ ላይ በተቃራኒው መስራት ይጀምራል።
ይህ መሰል ህግ ሞመንተም ወደሚባለው ሌላኛው ህግ ይወስደናል። የበለጠ እየጨመረ የሚቀጥል ፍጥነታዊ እንቅስቃሴ የአንድን ግለሰብ ሞመንተም የበለጠ ይጨምረዋል። ይህም መሰል ድርጊታዊ እንቅስቃሴ የበለጠ በተደጋገመ ቁጥር የግለሰቡ ባህሪ ወይም ልማድ ወደመሆን ያመራል። ከዚያም ይህ ሰው ራሱን ፈለገም አልፈለገም ምን ጊዜም በሞመንተም ውስጥ ያገኘዋል። «A body in motion will remain in motion» እንደተባለውም ቀልጣፋና ፈጣን አንቅስቃሴን ማዘውተር ይህን መሰል የቅልጥፍና ልማድ (Habit) ውስጥ የሚከት ይሆናል። አንድ ነገር ወደልማድ ደረጃ ከተሸጋገረ ደግሞ ከእኛ ጋር አብሮን ይዘልቃል። በአንፃሩ ደግሞ የስንፍናና የመጎተት ድግግሞሽ ያለው ሰው ይህንኑ ልማድ ያዳብረና ወደፊትም በዚሁ ሊቀጥል ይችላል። «A body at rest will remain at rest» እንደሚባለው ነው:: እናም የበዛ መጎተትና እረፍት ማልገምንና መዛግን ይፈጥራል። አዕምሮም ይዝጋል «frequent rest will bring frequent rust» እንደሚባለው ነው።
ዶ/ር አቡሽ አያሌው
አልፋና ኦሜጋ ቁጥር ፩ - ገጽ 17-19
Comments
Post a Comment