ይህ ሁለተኛ የኒውተን ህግ «የሽምጠጣ ህግ» ወይም ደግሞ «The law of acceleration» በመባል ይጠራል። በአንድ ግዑዝ ነገር ላይ ሀይል ብናሳርፍ ነገርየው የፍጥነት ለውጥ በማድረግ የመሸምጠጥ ዕደል ይኖረዋል የሚል ነው። ሽምጠጣ ማለት በፈረስ ግልቢያ ጊዜ ቀድሞ ከነበረው የፈረሱ ፍጥነት በላይ የበለጠ ፍጥነት ጨምሮ መጓዝን ያመሰክታል፡፡ እንዲሁም ደግሞ ሀይሌ ገብረስላሴና ቀነኒሳ በቀለ የአስር ሺህ ኪሎ ሜትር ሩጫ ላይ ለማሸነፍ የሚጠቀመብትን የመጨረሻ አጨራረስ ስንመለከት ወትሮ ሲሮጠብት ከነበረው የዙር ፍጥነት በላይ ከፍተኛ ሀይል በመጨመር ከፍተኛ የሆነ የፍጥነት ጭማሮ የሚያደርጉትም ሽምጠጣ ከዚህ ጋር የሚሄድ ነው። እንዲሁም አንድ መኪና ከአንደኛ ማርሽ ተነስቶ ወደ ሁለተኛ፣ ሶስተኛ፣ አራተኛና አምስተኛ ሊገባ በየማርሽ ቅየራ ውስጥ የበለጠ ነዳጅ በማቀጣጠልና የግፊት ሀይል በመፍጠር የፍጥነት ጭማሮ ይከሰታል። ይህ መሰሉ በየሰከንዱ የሚደረግ የሀይል ጭማሮና ከበፊቱ የበለጠ የፍጥነት ጭማሮ ወይም ሽምጠጣ «Acceleration» በመባል ይጠራል።
የሰው ልጆችም ይህ መሰል ሽምጠጣዊ አኗኗርና አሰራር አላቸው አንድ ሰው ሁልጊዜ በተለመደው ፍጥነታዊ እንቅስቅሴና ስኬት ላይ የሚቆይ ከሆነ በሌሎች ተወዳዳሪዎቹ ሊቀድምና ስራውም ሊበላሽበት ይችላል። በየጊዜው እየጨመረ ከሚመጣው የኑሮ ጫናም «inflation» ለማምለጥ ይከብደዋል። ተመሳሳይ ድርጊት የሚፈጥረው ነገር ቢኖር ተመሳሳይ ውጤት ነው። ሁልጊዜ ተመሳሳይ የሆነ ውጤትና ኑሮ ደግሞ ለግለለቡም ሆነ ለቤተሰቡ እንዲሁም ደግሞ ለመስርያ ቤት ሰራተኞች ይሰለቻል። አዕምሯችን የተፈጠረው ሁልጊዜ ከበፊቱ የተሻለ አኗኗርና አሰራር እንዲሁም ውጤትና ስኬትን ለማየት ነው፡፡ ይህ መሰል በየጊዜው የበለጠ እያደገ የሚሄድ ስኬታማነትና ለውጥ የበለጠ አስደሳችና አርኪ ነው፡፡
የሰዎች የስኬት ፍጥነት «Performance» በሚባለው የውጤታማነት መለኪያ መስፈርት ይለካል ይህ መሰል ስኬት ደግሞ ከጊዜ አንፃር ነው የሚታየው። የአንድ ሰው ወርሃዊ የስኬት መጠን ወይም ደግሞ ዓመታዊ የስኬት መጠን ማለትም «ፐርፎርማንስ» ከግለሰቡ ያለፈ ተመሳሳይ ጊዜ የስኬት ፍጥነት ጋር ሲወዳደር ተመሳሳይ ከሆነ የፐርፎርማንስ ፍጥነቱ ለውጥ አላመጣም ወይም ደግሞ የሽምጠጣ ውጤታማነት ውስጥ አልገባም ማለት ነው። ነገር ግን ይህ ግለሰብ በየዓመቱ የስኬታማነት ወይም የውጤታማነት ብልጫ ላይ የገባ ከሆነ የፐርፎርማንስ መጠኑ «Accelerate» አድርጓል ብለን እንናገራለን። እንዲሁ ደግሞ የአንዳንድ ግለሰቦች የዘንድሮው ውጤታማነታቸው ከባለፈው ጋር ሲነፃፀር ሊያንስ ከቻለ ፐርፎርማንሳቸው ወርዷል ወይም ደግሞ «Deaccelerate» አድርጓል ብለን አንናገራለን።
በመሆኑም ከሌሎች ተወዳዳሪዎቻችን ልቀን ለመገኘትና አንደ እነ ሐይሌና ቀነኒሳ ለማሸነፍ፣ ከኑሮ ጫና ውጭ ለመሆንና በህይወታችን የበለጠ ደስተኛ ሆኖ ለመገኘት ምንጊዜም በሽምጠጣ ፐርፎርማንስ (Accelerated performance) ውስጥ መገኘት መቻል አለብን። የሽምጠጣ ፍጥነት ወይም «Acceleration» መላው ዩኒቨርስ ሳይቀር የሚመራበት ህግ ነው። በአሁኑ ወቅትም ዩኒቨርሳችን በየሰከንዱ በከፍተኛ የሽምጠጣ ፍጥነት ውስጥ ወደፊትና ወደጐን እየተወረወረ ይገኛል።
ዶ/ር አቡሽ አያሌው
አልፋና ኦሜጋ ቁጥር ፩ - ገጽ 20-21
Comments
Post a Comment