ቻትጂፒቲን የፈጠረው ሳም አልትማን የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች ሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ላይ ቁጥጥር እንዲያደርጉ ጠየቀ። ቻትጂፒቲን የፈጠረው የኦፕንኤአይ ተቋም ዋና ኃላፊ ሳም በአሜሪካ ምክር ቤት ቃሉን በሰጠበት ወቅት ስለአዲሱ ቴክኖሎጂ ተስፋና ስጋት ገልጿል። በወራት ውስጥ ብዙ የኤአይ ሞዴሎች ገበያውን ተቀላቅለዋል።
ሳም እንዳለው ለኤአይ ተቋማት ፈቃድ የሚሰጥ አዲስ የመንግሥት ድርጅት ሊቋቋም ይገባል። ቻትጂፒቲ እና ሌሎችም እሱን የሚመስሉ መተግበሪያዎች ከሰው ጋር የሚመሳሰል መልስ ይሰጣሉ። መልሶቻቸው የተሳሳቱ የሚሆኑበትም ዕድል አለ። የ38 ዓመቱ ሳም ዘርፉን በተመለከተ ንግግሮች በማድረግ ይታወቃል። ኤአይ የሚያስነሳቸውን የሥነ ምግባር ጥያቄዎች ከግምት በማስገባትም ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግ ይጠይቃል። ኤአይ እንደ ኅትመት ሊሰፋ የሚችል ዘርፍ ቢሆንም አደጋ እንደሚጋርጥም አልሸሸገም። ኤአይ ምጣኔ ሀብት ላይ የሚያደርሰውን ጫና እንዲሁም የሰዎችን ሥራ ሊቀማ እንደሚችልም ባለሙያው ያስጠነቅቃል።
“ሥራ ሊጠፋ እንደሚችል በግልጽ መናገር አለብን” ይላል። በሌላ በኩል ኦፕንኤአይን ለመክሰስ መንገዶች እንዲመቻቹ የሚጠይቁም አሉ። ሳም በምክር ቤት ንግግሩ፣ ኤአይ በዴሞክራሲ ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ በተለይም በምርጫ ወቅት ስለሚሰራጭ ሐሰተኛ መረጃ ስጋቱን ገልጿል። ለኤአይ ተቋሞች ፍቃድ የሚሰጥ እንዲሁም የሚቀማ የመንግሥት ድርጅት አስፈላጊነቱንም አስረድቷል። እንደ ኦፕንኤአይ ያሉ ተቋማት በገለልተኛ ወገን ሊደረግ እንደሚገባም ገልጿል።
ሪፐብሊካኑ የምክር ቤት አባል ጆሽ ሀውሌይ ቴክኖሎጂ አብዮተኛ ቢሆንም “አቶሚክ ቦምብ” የሚሆንበትም ዕድል አለ ብለዋል። ዴሞክራቱ የምክር ቤት አባል። ሪቻርድ ብሉሜታል ደግሞ በኤአይ የተዋጠ የወደፊት ዓለምን አንፈልግም ብለዋል። “በጎው ከመጥፎው እንዲበልጥ መሥራት አለብን። ምክር ቤቱ ምርጫ አለው። ማኅበራዊ ሚዲያን ሳንቆጣጠር ከእጃችን ወጥቷል” ሲሉም አክለዋል። አዲስ ዘርፉን የሚቋቋም ድርጅት ሊመሠረት ይችላል። ሆኖም ቴክኖሎጂው ከሚሄድበት ፍጥነት አንጻር ሕግ አውጪዎች ምን ያህል ርቀት ይሄዳሉ የሚለው አጠያያቂ ነው።
ምንጭ፦
BBC Amharic - https://www.bbc.com/amharic/articles/cd1kvgk8p02o
Comments
Post a Comment