በተለያዩ የሆሊውድ ሳይንሳዊ ልብወለድ ፊልሞች ላይ እጅግ ግዙፍ የሆኑ የህዋ ላይ መጓጓዣ ወይም ስፔስሺፖችን አይተናል፡፡ ታድያ እነዚህን ግዙፍ የህዋ ላይ መጓጓዣዎች ከፊልምም ባሻገር እውን እንዲሆኑ የሚያስችል እንቅስቃሴ በቻይና ተጀምሯል፡፡ ሀገሪቱ 1 ኪ.ሜ የሚረዝም የህዋ ላይ መጓጓዣን መስራት ስለሚቻልበት መንገድ ጥናት ጀምራለች።
ስራውን አስመልክቶ ይፋ የተደረገው ጽሑፍ እንዳመላከተው ይህ ግዙፍ የህዋ ላይ መጓጓዣ ወደፊት የህዋ ሀብትን ለመጠቀም፣ ድብቁን የዩኒቨርስ ከባቢ ለማሰስ እንዲሁም ረዘም ላለ ጊዜ ለመኖር የሚያገለግል ነው፡፡ አሁን ላይ መጓጓዣውን አስመልክቶ 2.3 ሚሊዮን ዶላር የሚያስወጣ የአዋጭነት ጥናት ለማከናወን ሲታቀድ ተመራማሪዎችም ወደ ህዋ ተልኮ ለግንባታው የሚውለውን ግብዓት በሚቀንስ መልኩ ቀለል ያለ ንድፍ እንዲሰሩ ይፈለጋል፡፡ ግን ይቻላል?
ይህን የሚያክል የህዋ ላይ መጓጓዣ መስራቱ በሳይንሳዊ ልብ ወለድ ፊልሞች ላይ ብቻ የሚሳካ ነገር ቢመስልም የዘርፉ ተመራማሪዎች ግን ከሳይንስ አንፃር እንዳይሳካ የሚያደርግ ተግዳሮት እንደሌለው ይገልፃሉ፡፡ ሆኖም በእንዲህ አይነት ግንባታ ላይ አንዱ ተግዳሮት ከስራው ግዝፈት ጋር ተያይዞ የሚመጣ የምህንድስና ስራ ነው፡፡ ሌላውና ትልቁ ተግዳሮት ግን የወጪው ጉዳይ ነው፡፡ በተለይም የግንባታ ቁሳቁሰሶችን ወደ ህዋ ማጓጓዙ ሲበዛ ውድ ነው፡፡ ለምሳሌ ወደ ጎን 110 ሜትር የሚረዝመው ዓለም አቀፉ የህዋ ምርምር ጣብያን (ISS) ለመገንባት 100 ቢሊዮን ዶላር ፈጅቷል፡፡ አዲሱ እቅድ ከዚህ 10 እጥፍ የሚረዝም አካል መገንባት መሆኑን ከግምት ስናስገባ ወጪውን ጭንቅላት የሚያዞር ያደርገዋል፡፡ የህዋ ላይ ማጓጓዣው ሰዎችን እንዲይዝ ተደርጎ የሚሰራ ከሆነ ደግሞ ወጪውን ይባስ ያንረዋል፡፡
ነገር ግን ወጪው በዋናነት የህዋ ላይ መጓጓዣው እንዲገነባ ከታሰበበት ንድፍ ጋር ይያያዛል፡፡ የግንባታ ስልቶችም እንዲሁ ወጪውን ሊቀንሱት ይችላሉ፡፡ በተለይ በ3ዲ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ከመሬት ውጪ የሚገኝ ግብአትን ተጠቅሞ መዋቅሩን መስራት የተለመደው የተፈበረኩ አካላትን ከመሬት አስልኮ እዚያው ህዋ ላይ የመገጣጠም ስልትን ሊቀይር ይችላል፡፡ በሌላ መልኩ ከመሬት አንፃር ጨረቃ ላይ ያለው የስበት ኃይል አነስተኛ በመሆኑ ከዚያ ግብዓቶችን አስፈንጥሮ መውሰድ ቀለል ያለ ነው፡፡
ከግንታው ባሻገር ግን ይህን አይነት ግዙፍ አካል ለሌሎች ችግሮችም ተጋላጭ ነው፡፡ በዚህ መጠን የገዘፈ የህዋ ላይ መጓጓዣ በሚንቀሳቀስበት እና ከሌሎች መሰል መጓጓዣዎች ጋርም በሚነካካበት ወቅት የሚገጥመው ኃይል በመጓጓዣው ውስጥ በቶሎ የማይቆም ከፍተኛ መንቀጥቀጥ እንዲነሳና መጓጓዣው እንዲጣመምም ጭምር ሊያደርገው ስለሚችል ይህን መቆጣጠርያ ቴክኖሎጂ ያስፈልገዋለ፡፡
በተጨማሪም የህዋ ላይ መጓጓዣው ከመሬት ርቆ የሚንሳፈፍበት ርቀትም እንዲሁ የራሱ ተግዳሮት አለው፡፡ መጓጓዣው ወደ ምድር በቀረበ ቁጥር የሚጎትተው ኃይል እያየለ ስለሚመጣ እራሱን ከዚህ ለማውጣት ሞተሮቹን ተጠቅሞ በተቃራኒ አቅጣጫ ራሱን መግፋት አለበት፤ ይህ ደግሞ ከፍተኛ ነዳጅን ይጠይቃል፡፡ በሌላ መልኩ ከምድር ርቆ በሄደ ቁጥር ወጪውም በጣም እየናረ ይመጣል፡፡ በዚያ ላይ ከከባቢ አየር በራቁ ቁጥር ጨረሩም ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱ በመጓጓዣው ውስጥ ሰዎች ካሉ ለእነርሱ አደገኛ ይሆንባቸዋል፡፡
ምንጭ፦ላይቭ ሳይንስ
Comments
Post a Comment