የተጣራ የወደፊት ጉዞ ለማድረግ የተጣራ የወደፊት ሀይል ያስፈልጋል። ይህም ማለት ደግሞ ወደፊት እንደተፈለገው ለመወርወር ገፍታሪው ሀይል ከጐታቹ ሀይል መብለጥ መቻል አለበት። ይህ መሰል የተጣራ የወደፊት ሀይል (Positive net force) በመባል ይጠራል። በአንፃሩ ደግሞ ወደፊት የሚገፈትረው ሀይል ወደኋላ ከሚስበው ሀይል የሚያንስ ከሆነ የተጣራው ሀይል ወደ ኋላ የሚገትት ስለሚሆን (Negative net force) የሚል መጠሪያ ይኖረዋል፡፡
በመሆኑም አንድ ሰው በህይወቱ ወደፊት በስኬት ጉዞ ውስጥ ለመገስገስ ውስጣዊ የግፊት ሀይል እንዳለው ሁሉ በውስጡም ሆነ በዙራያው ወደኋላ የሚጐትቱት ሀይሎች አሉ። እነህ ሀይሎች የግለሰቡን ትኩረት የሚበትኑ፣ የይቻላል እምነቱን የሚሸረሽሩ፣ ሞራሉን የሚከሰክሱ ወይም ደግሞ ከመነቃቃትና ፍጥነታዊ ድርጊት ይልቅ ማልገምንና ስንፍናን የሚፈጥሩ ናቸው። ይህ መሰል ግለሰብም ወደፊት የመወርወርና ስኬታማነቱን የሚያቀጣጥል እንቅስቃሴው በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ገዳቢ ነገሮች እንዲገደብ ይሆናል። ወደፊት ከመሄድ ይልቅም ባለበት እንዲቆም ይገደዳል ወይም ደግሞ ወደኋላ እንዲንሽራተት ሊሆን ይችላል። ወይም የወደፊት ስኬቱ ረጅም ጊዜን ሊወስድና ሊጓተት ሁሉ ይችላል።
በአንተም የዕለት በዕለት ህይወት ውስጥ ያሉት ሁለት ሀይሎች በዚህ የሚመሰሉ ናቸው። ወደፊት የሚገፈትሩና ወደኋላ የሚጐትቱ። በመሆኑም ወደፊት በስኬት ለመገስገስ የምትፈልግ ከሆነ በተቻለ መጠን የወደፊት ገፍታሪ ሀይሎችህን ምጣኔ በጥራትም ሆነ በብዛት መጨመር የሚጠበቅብህ ሲሆን ወደኋላ የሚገትቱ ውስጣዊ የአንተነት አስተሳሰቦችንና ልማዶችን እንዲሁም ውጫዊ የስራ መሰናክል የሆኑ ሰዎችንም ሆነ አካባቢን መቀነስ ወይም ማስወገድ መቻል አለብህ። በውስጥህ ሁለት ሀይሎች አሉ Motivational force (አነቃቂና አትጊ ሀይል) እንዲሁም Demotivational force (ጐታችና አስናፊ ሀይል)። የአንተ የወደፊት ፈጣን የስኬት ግስጋሴም በሁለቱ የሀይል ሚዛኖች ውስጥ ያርፋል።
ዶክተር አቡሽ አያሌው
አልፋና ኦሜጋ ቁጥር 1 - ገጽ 25-27
Comments
Post a Comment