ኒውክለር ቴክኖሎጂ - ክፍል ፩

 

    የማህበረሰብንና የሀገርን ችግር ለመቅረፍ በቴክኖሎጂው እድገት ላይ አዎንታዊ ለውጥ እና ሁለንተናዊ እድገትን ለማምጣት በርካቶች የራሳቸውን አሻራ ጥለው አልፈዋል፡፡ ታዲያ ይህ የሰው ልጅ የህይወት ተሞክሮ ያበረከተው ድልብ እውቀት የሚማርባቸው ተምሮባቸው የሚጠቀመውም ተጠቅሞባቸው አሁን ላለንበት ዓለም እንደመሸጋገሪያ ድልድይ ሆነዋል፡፡ ቴክኖሎጂ የመጣበት ሰንሰለታማ እድገት ለዛሬው የቴክኖሎጂ ውጤቶች መስፋፋት ምክንያት ሆኗል፡፡ በቀደሙት ጊዜያት ተተግብረው እስከ አሁን ለሰው ልጅ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እየሰጡ ካሉ ቴክኖሎጂዎች መካከል ኒኩለር ቴክኖሎጂ ተጠቃሽ ነው፡፡

    ዓለም ላይ የሚገኙ ማናቸውም የማናያቸውም ሆነ የምናያቸው ነገሮች በሙሉ ከአተም የተሰሩ ናቸው፡፡ አተም በውስጡ ሶስት የተለያዩ ነገሮችን ማለትም ፕሮቶን፣ ኒውትሮን እና ኤሌክትሮንን ይዛል፡፡ ፕሮቶንና ኒውትሮን በአተም የመካከለኛው ክፍል ውስጥ በአንድ ላይ ተሰብስበው የሚገኙ ሲሆን ኤሌክትሮን ደግሞ በኒኩለስ ዙሪያ ኤሌክትሮኖች በተለያየ ርቀት ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ አተም ሲባል ከነዚህ ሶስት ነገሮች የተሰራ ነው፡፡ ነገር ግን በተፈጥሮ አንዳንድ አተሞች ወደ ተለያየ የቁስ አካል የመለወጥ ባህሪ አላቸው፡፡ እንደዚህ አይነት አተሞች ራዲዮ አይሶቶፕስ (የአንድ አተም ጨረር የማመንጨት ወይም ተግባራቸው ከፍተኛ የሆኑ በተፈጥሮ አልያም በሰው ሰራሽ ዘዴ የምናመርታቸው የአተም አይነቶች) ይባላሉ፡፡

    ኒኩለር ኢነርጂ ሲባል በኒኩለስ ውስጥ ፕሮቶንና ኒውትሮን አንድ ላይ በሚሆኑበት ጊዜ በመሀከላቸው አምቀው የያዙት ትልቅ ሀይል አለ፡፡ ይህ ሀይል ለተለያዩ አገልግሎቶች ሊውል የሚችል ሲሆን ሀይሉን አውጥተን የምንጠቀምበት ዘዴ ኒኩለር ቴክኖሎጂ ይባላል፡፡

    የኒኩለር ሀይል የአተሚክ ኒኩለስ ኢነርጂ ማለት ሲሆን ከዚህ ቅንጣት ከሆነ ነገር ሀይልን (ኢነርጂን) ለማውጣት ደግሞ ፊዥን እና ፊዩዥን የሚባሉ ሁለት ሂደቶች ያስፈልጋሉ። ፊዥን ማለት ትልቅ የሆነን አተም የሚከፋፍል እና ከዛ ውስጥ የሚወጣውን ኢነርጂ መጠቀም የሚያስችል ሲሆን ፊዩዥን ደግሞ ሁለት የተለያዩ አተሞች እርስ እርሳቸው በሚዋሃዱበት ጊዜ የምናገኘው ኢነርጂ ማለት ነው። ለምሳሌ ፀሀይ አሁን የምትሰጠን ሙቀት እና ብርሀን ሀይድሮጂን አተሞች በአንድ ላይ ሲጠናከሩ በመሃከላቸው ሲዋሀዱ በሚፈጠር ሀይል ነው፡፡ ፊውዥንን ለመጠቀም ትንሽ ከበድ ስለሚል ተግባር ላይ በአብዛኛው ተግባራዊ የሚደረገው ፊዥን ነው። ምክንያቱም አንድ ትልቅ አተም በሚለያይበት ጊዜ የሚፈጠሩት ክብደቶች ሲደመሩ ከመጀመሪያው ጋር እኩል አይመጣም፤ ለዚህም ነው የኒኩለር ሀይሉም፣ የኒኩለር ቦምቡም ማንኛውም ነገር በዚህ በኒኩለር ፊዥን ነው የምናገኘው።

ይቀጥላል...

ምንጭ፦

  1. ቴክ ሳይንስ መጽሔት
  2. ታፈሰ ሙሉነህ - የኑክሊየር ሃይል ታሪካዊ ግኝቱ [1993]


Comments