አተም ለብዙ ዓመታት የኖረ ሲሆን የጥንታዊ ግሪክ ፈላስፋዎች በመጀመሪያ ሁሉም ቁሶች በማይታይ ቅንጣት የተገናኙት ሁሉ አተም ይባላሉ በማለት ሃሳባቸውን አሳደጉ። አተም ማለት አቶሞስ ከሚል የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙ ሊከፈል የማይችል (indivisible) ማለት ነው።
መጀመሪያ ኒኩለር ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ የዋለው በበጎ ጎኑ አይደለም። የሁለተኛው የአለም ጦርነት ከመጀመሩ በፊት የተለያዩ የፊዚክስ ባለሙያዎች ከኒኩለር መዋቅር ጋር በተያያዘ ብዙ ጥናቶችን አካሄደው ነበር። የኒኩለር ሀይልን እንዴት ማግኘት እንደሚችሉ እና የአቶሚክ መዋቅር ምን ይመስል እንደነበር ትኩረት ሰጥተው ያጠኑት ነበር።
1900 አካባቢ የኒኩለር ፊዚክስ አባት የሚባለው አርነስት ራዘር ፎርድ አተምን ለጥሩ ነገር መጠቀም ብንችል ለተለያዩ አገልግሎቶች ሊውል የሚችል ከፍተኛ ኢነርጂ ማግኘት እንደሚቻል ተናግሮ ነበር። ፎርድ ይህን በተናገረ ከአንድ አመት በኋላ ታዋቂው የፊዚክስ ባለሙያ አልበርት አንስታይን E=MC2 (አንድ ቁስ አካል ወደ ሀይል መቀየር ይችላል በተቃራኒው ደግሞ አንድ ሀይል ወደ ቁስ መቀየር ይችላል) የሚለውን ፅንሰ ሀሳብ አቀረበ። ነገር ግን ይህንን ፅንሰ ሀሳብ ለመረዳት 35 ዓመታት ያህል ፈጅቷል።
በ1934 ኢንሪኮ ፈርሚ የተባለ የጣልያን የፊዚክስ ባለሙያ ሮም ውስጥ ዩራኒየምን (ከባድ አተምን) በኒውትሮን በመምታት ሙከራ አካሂዶ እጅግ ያልጠበቀው ነገር አጋጥሞት ነበር፡፡ ይኸውም አተሙ ወደ ሁለት የተለያየ ነገረ ነበር የተከፈለው ነገር ግን ለሁለት የተከፈሉትን አተሞች ሲደምራቸው ክብደታቸው ከመጀመሪያው ጋር እኩል ሆኖ አላገኘውም፡፡ ስለዚህ የሁለቱ ክብደት ተደምሮ ከመጀመሪያው ጋር እኩል ካልመጣ የጠፋ ክብደት እንዳለ በመረዳት ከሰላሳ አምስት አመት በፊት አንስታይ የተናገረውን ሀሳብ E=MC2 የሚለውን ፅንሰ ሀሳብ ሊረዳው ችሏል፡፡ ከዛም በኋላ ይሄው የጣልያኑ ፊዚስት ችካጎ ውስጥ ከአንስታይን ጋር የፊዚክስ ንድፈ ሀሳብ ውይይት አድርገው ዩራኒየምን (ከባድ አተምን) ከፕሮቶን ጋር በመምታት ተከታታይ የሆነ ውህደት በማድረግ የአተምን ሀይል ማዉጣት እንደሚችሉ ለመረዳት በቁ፡፡ በማስከተል እ.ኤ.አ በ1942 የመጀመሪያውን የኒኩለር ማብለያ(reactor) በችካጎ ዩኒቨርሲቲ ለሙከራ ሲሰራ በትክክል ከአተም ውስጥ ሀይል ማግኘት እንደሚችሉ አረጋገጡ።
ከሶስት አመት በኋላ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት አሜሪካ ይህንን ሀይል ለጦር መሳሪያ ለመጠቀም ኒኩለር ቦምብ በመስራት ሜክሲኮ አከባቢ ፍተሻ አደረገች፡፡ ፍተሻ ከተደረገ ከአንድ ወር በኋላ ጃፓን ውስጥ ሄሮሽማ ላይ (a little boy) ትንሹ ልጅ በሚል በሁለተኛው የአለም ጦርነት ጊዜ የመጀመሪያውን ኒኩለር ቦንብ ጣለች፡፡ ከአንድ ወር በኋላ በድጋሚ ከበፊቱ ከፍ ያለ (the fat man) ወፍራሙ ሰውዬ በሚል ናጋሳኪ ላይ ተጣለ፡፡ ስለዚህ የአንስታይንን ፅንሰ ሀሳብ በመከተል ኒኩለር በመጀመሪያ ተግባር ላይ የዋለው በቦንብ ደረጃ ነው፡፡
ከዛ በኋላ በወቅቱ የነበሩት የአሜሪካን ፕሬዝዳንት አተምን ለጦርነት ሳይሆን ለሰላም፣ ለምርት እና ለእድገት በሚል የፖለቲካ ሰዎችንና የፊዚክስ ሰዎችን በማስተባብር atom for peace (አተምን ለሰላም) የሚል እንቅስቃሴ አስጀመሩ፡፡ እ.ኤ.አ በ 1946 አሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ አተሚክ ኢነርጂ ኮሚሽን አቋቋመች። ኮሚሽኑ የሚሰሩ የኒኩለር ማብለያዎች ለጦርነት ሳይሆን ለሰላም እየዋሉ እንደሆነ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በዚያን ወቅት ኃያላን ሀገራት የሚባሉት የሚፎካከሩበት ጊዜ ስለነበረ ሩሲያ እና ፈረንሳይ ኒኩለር ለመስራት ሙከራ አደረጉ፡፡ በተለይም አሜሪካ እና ሩሲያ በጣም ተፎካካሪዎች ነበሩ፡፡ አሜሪካ የመጀመሪያውን ኒኩለር ስትሰራ ሩሲያ የተለያዩ መረጃዎችን በማሰባሰብ ከጎን ኒኩለር መስራት ጀምራ ነበር፡፡ ነገር ግን አተምን ለበጎ ነገር በማዋል ረገድ ሩሲያ የመጀመሪያውን ደረጃ ትወስዳለች፡፡
ይቀጥላል...
ምንጭ፦
- ቴክ ሳይንስ መጽሔት
- ታፈሰ ሙሉነህ - የኑክሊየር ሃይል ታሪካዊ ግኝቱ [1993]
Comments
Post a Comment