ዓለም በላቀ የቴክኖሎጂ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ቴክኖሎጂ በትምህርት፣ በመከላከያ፣ በግብርና፣ በትራንስፖርትም ሆነ የእያንዳንዷ ሕይወታችን አካል ሆኗል። ያለ ቴክኖሎጂ ሕይወት የማይታሰብ በሚመስል ሁኔታ የሰው ልጅ ህይወት እና ቴክኖሎጂ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ሆነዋል። ከማንኛውም የታሪክ ዘመን በላይ የሰው ልጅ በቴክኖሎጂ ላይ ጥገኛ ሆኗል። የትዳር አጋርንም እንኳን ለማግኘት ቴክኖሎጂ ዋነኛ መንገድ ከሆነ ከራረመ።
ይህንን ሁሉ ስናይ የሰው ልጅ ከቴክኖሎጂ ጋር ያለው ግንኙነት ምን ዓይነት ይሆን? የሚለውን ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም። መልሱም ውስብስብ የሚል ነው። ከተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች መብዛት ጋር ተያይዞ ዓለም የጠበበች መንደር ብትመስልም፣ በርካቶች በብቸኝነት ኑሯቸውን የሚገፉባት ሆናለች። በቴክኖሎጂ እገዛ ምክንያት ምርታማነት ቢጨምርም በርካቶች በሥራ ድካም መጠውለግ የሚሰማቸው ሁኔታ ተፈጥሯል። ሌላ እንጨምር፣ የግል መረጃዎቻችንን ለመጠበቅ በርካታ መተግበሪያዎች ቢኖሩም እንዲህ መረጃዎቻችን ለስርቆት የተጋለጡበት ሁኔታም ሆነ ወቅት እንዳሁኑ ዘመን የለም።
ምንም እንኳን ከቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋር ያለን ግንኙነት የተወሳሰበ ቢሆንም፣ አንዳንድ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ለዓለማችን ያመጡት መልካም ውጤት ላይ ጥያቄ አይነሳም። ለምሳሌም ያህል በቅርቡ መድኃኒትን የሚቋቋሙ እና ገዳይ የሆኑትን የሆስፒታል ጎጂ ህዋሳትን የሚያጠፋ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) እገዛ የተሠራው ፀረ ባክቴሪያ (አንቲ ባዮቲክ) ቀመር ተጠቃሽ ነው። በተጨማሪም ካርቦንዳይኦክሳይድን ከአየር ላይ መጥጠው የሚያስወግዱ ማሽኖች የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ተጽዕኖ ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት ትልቅ ዕገዛም ሊሆኑ ይችላሉ። የቪዲዮ ጨዋታዎች እና ፊልሞችም የሰው ልጆችን በማዝናናት የራሳቸውን አሻራ አሳርፈዋል።
በሌላ በኩል ከቴክኖሎጂ ጋር የተገናኙ ውዝግቦች የበርካታ ሚዲያዎች አርዕስተ ዜና ሆነው ታይተዋል። ስለ መረጃ ጥሰቶች፣ የሳይበር ጥቃቶች እንዲሁም በበይነ መረብ የሚፈጸሙ ዘግናኝ የጥቃት ታሪኮች በተደጋጋሚ በየሚዲያዎቹ ሲወጡም ይታያል። በዩናይትድ ኪንግደም የተሳሳተ የኮምፒውተር አካውንቲንግ መተግበሪያ (ሶፍትዌር) ከፖስታ ቤት ቅርንጫፎች ገንዘብ መጥፋቱን በማሳየቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ሠራተኞች በማጭበርበር ክስ ተመስርቶባቸው ነበር። ይህም ከሰዎች በላይ በቴክኖሎጂ ላይ ጭፍን ያለ እምነት አሳድረናል በሚልም ብሔራዊ ቁጣን ፈጥሯል። “እንደ ሁሉም ነገር ቴክኖሎጂ አሉታዊ ጎን አለው። ቴክኖሎጂ በሁለቱም በኩል የተሳለ ሰይፍ ነው” ሲሉም አንጋፋው የሲልከን ቫሊ ኩባንያ ባለሙያ ፕሮፌሰር ማይክ ማሎን ያስረዳሉ።
ቀደም ሲል እንዳልነው ቴክኖሎጂ ውስብስብ ነው። የቴክኖሎጂን አሉታዊ ጎኖች የሰዎች ሕይወት ላይ ከፍተኛ ቀውስን ከማስከተላቸው ጋር ተያይዞ ሰዎች በቴክኖሎጂ ላይ ያላቸው እምነት እየተሸረሸረ ይሆን? የሚለውን ጥያቄ ያጭራል። ከወትሮው በበለጠ አይደለም ሲሉ የቴክኖሎጂ ጅምሮችን የሚደግፈው ፓሺን ካፒታል የተሰኘው ኩባንያ ሠራተኛ ኢሊን ቡርቢጅ ያስረዳሉ። “ሁኔታው አዙሪት ነው ብዬ አስባለሁ” ይላሉ “ከዚህ ቀደምም በመረጃ ግላዊነት፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ)፣ ሮቦቲክስ፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎች፣ ከደኅንነት ጋር በተያያዘ ባለፉት ዓመታት የተወያየንባቸው ናቸው” ይላሉ። እነዚህ ውይይቶችም መቀጠል እንዳለባቸው ያምናሉ። “ሸማቾች ወይም ተጠቃሚዎች እና ተቋማት ስለሚቀበሏቸው ቴክኖሎጂዎች የበለጠ ጠንቃቃ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል። እንዲሁም ተቆጣጣሪዎች ትኩረታቸውን የት ላይ ማድረግ እንዳለባቸውም እንዲያስቡ ያደርጋል” ሲሉም ይገልጻሉ። በማስታወቂያ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ታላቅ ስም ያላቸው ሰር ማርቲን በበኩላቸው “ሁሉም ሰው ቴክኖሎጂን ይጠቀማል። በቴክኖሎጂ ላይ ያለንን እምነት እያጣን ነው ማለት ስህተት ነው” ይላሉ።
ነገር ግን ሰዎች ቴክኖሎጂ ሊያስከትለው የሚችለውን መዘዝ እየፈሩ እንደሆነ ያስረዳል። በተለይም የሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) መሳሪያዎች በሥራዎች ላይ በፍጥነት ከመስፋፋታቸው ጋር ተያይዞ በርካቶች ስጋት አድሮባቸዋል።
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት መሠረት 40 በመቶ የሚሆኑ የሥራ ዘርፎች በሰው ሰራሽ አስተውሎት ተፅእኖ እንደሚያርፍባቸው ነው። የራሳቸውን የሥራ ዘርፍ ማስታወቂያንም በማንሳት ለውጡን የሚያስረዱት “ከዚህ ቀደም ማስታወቂያ ለመሥራት የሚፈጀው ጊዜ ከሦስት ሳምንት ወደ ሦስት ሰዓት መቀነሱን” ዋቢ በማድረግ ነው።
ሰዎች ከሰው ሰራሽ አስተውሎት ጋር በተያያዘ የሚፈሩት ሥራቸውን ማጣታቸው ብቻ አይደለም። ወደፊት ሰዎችን በተመለከተ መሠረታዊ ውሳኔዎችን የሚያስተላልፉት እነዚህ መሳሪያዎች ሊሆኑ ይችላሉ የሚለው ሌላ ስጋት እንደሆነም ያስረዳል። ምናልባትም ስለ ጤና አጠባበቅ ወይም በፍርድ ሂደት ወቅት እነዚህ መሳሪያዎች ወሳኝ ሊሆኑ ይችላሉ የሚለው፣ መድልዎ እና መገለልን ሊያመጡ ይችላሉ የሚል ስጋትን እየፈጠረ ነው። ከዚያም ባለፈ እነዚህ መሳሪያዎች የሠለጠኑበት መረጃ የማን ነው? የሚለው ላይ ጥያቄዎች መነሳታቸው አልቀረም። በተጨማሪም ከቁጥጥር ውጪ በሆኑ ማሽኖች የሰው ልጅ ህልውና ላይ ጥፋት ይጋርጣሉ የሚለውም አንዳንዶች የሚያነሱት ጉዳይ ሆኗል።
የቴክኖሎጂ ዘርፉን በቅርበት የሚከታተሉት ተንታኝ ፓውሎ ፔስካቶር በበኩላቸው “በመሠረታዊነት የቴክኖሎጂ ውጤቶች ችግር ቢኖርባቸው የሰው ልጆች መጠቀማቸውን ያቆሙ ነበር። ሊያቆሙም ይገባል” ይላሉ። ነገር ግን ከዓለም፣ ከሥራ ባልደረቦች፣ ከጓደኞች፣ ከቤተሰብ ጋር ላለመቆራረጥ እንዲሁም አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታል ለመቀየር ከሚፈልጉ መንግሥታትም ጭምር ጫና ሊኖር እንደሚችል ይናገራሉ። ራሳቸው የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችስ? ትልልቆቹ የአሜሪካ ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በቅርብ ወራት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን አባረዋል። የቴስላ እና የቀድሞው ትዊተር የአሁኑ ኤክስ ባለቤት ኤሎን መስክ የኮቪድ-19 ወረረሽኝ ጫና መቀነሱን ተከትሎ ሠራተኞቻቸው ወደ ቢሮ መጥተው ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ከጠሩት ቀዳሚዎቹ መካከል አንዱ ነበሩ።
እነዚህ የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪዎች ለሠራተኞቻቸው የበለጠ ምቹነትን እየነፈጉ እንደሆነ ሥራ ፈጣሪው ቶማስ ሃልጋስ ይናገራሉ። “የቴክሎጂ ኩባንያ ሠራተኞች ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በፊት ሥራቸው በጣም የተመቻቸ ነበር” ይላሉ። “ሰዎች ጉግል የሥራ ቦታ ሳይሆን ጡረታ የሚወጣበት ስፍራ ነው ይሉ ነበር። ያ ጊዜ አልፏል” በማለትም ያስረዳሉ።
ሃልጋስ ትልልቅ ተግባራትን ለማከናወን ምኞት ያላቸው ወጣት እና የቴክኖሎጂ ኩባንያ አለቃ ናቸው። የመጀመሪያውን የቴክኖሎጂ ጅምር ኩባንያ ለቀድሞው ትዊተር ከሸጡ በኋላ 2 ሚሊዮን ዶላር ያገኙ ሲሆን፣ ሁለተኛውን መተግበሪያዎችን የሚሰራ ሱትሮ የተሰኘ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የሚታገዝ የቴክኖሎጂ ኩባንያንም መሥርተዋል። “የቴክኖሎጂ ሠራተኞችን መተካት እንደማንችል እናስብ ነበር። በአሁኑ ወቅት ልንተካ ከምንችለው ሰዎች መካከል ነን” የሚሉት ፔስካቶር ራሳቸው የፈጠሩት የሰው ሰራሽ አስተውሎት መሳሪያም አንዱ ሰዎችን የሚተካ ነው። “ከዚህም ጋር ተያይዞ በርካቶች የህልውና ቀውሶች እያጋጠማቸው ነው” ይላሉ። የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪንም ሆነ የሰው ልጅ አስተውሎትን በቅርበት ሲከታተሉ ከነበሩት መካከል አንዱ የሆኑት ፔስካቶር ሰዎች የሚፈልጓቸውን መረጃዎችንም ሆነ ለጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጠው ቻት ጂፒቲ መምጣት የዘርፉ ባለሙያዎችንም ጭምር ያስደነቀ እንደሆነም ያስረዳሉ።
ቻት ጂፒቲ ተግባራዊ ከሆነ አንድ ዓመት የሆነው ሲሆን፣ ይፋ በተደረገ በወራት ውስጥም ሠልጣኝ ጠበቆች የሚፈተኑትን ‘ባር’ የተሰኘውን ፈተናም ማለፍ ችሏል። ቻት ጂፒቲን የፈጠረው ኦፕን ኤይ የተሰኘው ተቋም ኃላፊ ሳም አልትማን በ2024 የምናያቸው ለውጦች የቀደመውን ስሪት “ጊዜው ያለፈበት” ያደርጉታል ሲሉም ያስረዳሉ።
የቴክኖሎጂ ውጤቶች ፈጠራ ቀዝቀዝ ማለት ይገባው ይሆን?
በቅርቡ በሕዝብ ግንኙነት ላይ የሚሠራው ኤደልማን ባደረገው ጥናት መሠረት 52 በመቶ የሚሆኑት የዩናይትድ ኪንግደም ዜጎች የቴክኖሎጂ ፈጣራ በጣም በፍጥነት እያደገ ነው ብለው እንደሚያምኑ አሳይቷል። በተጨማሪም 70 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች አዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ቀስ ብለው ማዳበር እንዳለባቸው አስተያየታቸውን መስጠታቸውን በጥናቱ ላይ ሰፍሯል። እነዚህ ሁኔታዎች ተግባራዊ የመሆን ዕድላቸው ኢምንት ነው። ምክንያቱም የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዘርፍ እያጎረፈ ያለው ገንዘብ አንዲሁም መፍጠር የቻለው ኃይል ሁኔታዎች በተቃራኒው እንደሚሄዱ አመላካች ነው። ሆኖም የቴክኖሎጂ መዘዞችን አስመልክቶ የሚደረጉት ሕዝባዊ ውይይቶች ጠቃሚ እንደሆኑ ፕሮፌሰር ማሎን ያስረዳሉ። አክለውም “ከእንግዲህ በጭፍን አዲስ ቴክኖሎጂን እየተቀበልን አይደለም። ይህ ጥሩ ነገር ነው” ይላሉ።
ምንጭ፦
BBC Amharic - https://www.bbc.com/amharic/articles/c72g1glle3jo
Comments
Post a Comment