አንድ የአሜሪካ ኩባንያ ጨረቃ ላይ መንኮራኩር በማሳረፍ የመጀመሪያው የንግድ ኩባንያ በመሆን ታሪክ ሠራ። ሂውስተን መቀጫውን ያደረገው ኢንትዩቲቭ ማሽንስ (Intuitive Machines) ኦዲሴየስ የተሰኘውን ሮቦት በጨረቃ ደቡብ አቅጣጫ አሳርፏል። ሮቦቱ ማረፉን ለማረጋገጥ ተቆጣጣሪዎች ጥቂት ደቂቃዎችን ቢወስድባቸውም የማታ ማታ መልዕክት አግኝተዋል።
የበረራ ዳይሬክተሩ ቲም ክራይን "እኛ የምናረጋግጠው ያለ ጥርጥር መሳሪያዎቻችን በጨረቃ ላይ መሆናቸውን እና መረጃ እያስተላለፍን መሆኑን ነው” ብለዋል። ዜናውን ተከትሎ የኩባንያው ሠራተኞች ደስታቸውን በጭብጨባ ገልጸዋል። ዜናው ለንግድ ኩባንያዎች ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለአሜሪካ የጠፈር ፕሮግራምም መሰረታዊ ነው ተብሏል። ኢንትዩቲቭ ማሽንስ የአሜሪካን የግማሽ ምዕተ ዓመት ከጨረቃ ውጭ የመሆን ታሪክ ቀይሮታል። የአሜሪካ ንብረት በጨረቃ ላይ ያረፈው በአውሮፓውያኑ 1977 በመጨረሻው የአፖሎ ተልዕኮ ወቅት ነው።
የአሜሪካ የጠፈር ኤጀንሲ ናሳ በኦዲሲየስ ላይ ለስድስት ሳይንሳዊ መሳሪያዎች የሚሆን ቦታ ገዝቶ ነበር። ዋና አስተዳዳሪው ቢል ኔልሰን “ድል አድራጊ” በማለት ለገለጹት ተልዕኮ ለኢንትዩቲቭ ማሽንስ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል። "አሜሪካ ወደ ጨረቃ ተመልሳለች። ዛሬ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የንግድ ኩባንያ - የአሜሪካ ኩባንያ - ጉዞውን ጀምሮ አሳክቷል። እናም ዛሬ የናሳ የንግድ አጋርነትን ኃይል እና ተስፋ የሚያሳይ ቀን ነው" ብለዋል።
ቁልቁል መውረድ ከመጀመሩ በፊት ተቆጣጣሪዎች ተልዕኮውን ሊያስቆም የሚችልን የቴክኒክ ችግር መቋቋም ነበረባቸው ተብሏል። ከፍታ እና ፍጥነት ማስላት የሚችለው የኦዲሴየስ ሬንጅ ሌዘርስ በትክክል አይሠሩም ነበር። እንደ ዕድል ሆኖ የናሳ የተወሰኑ የሙከራ ሌዘሮች የነበሩ በመሆናቸው መሐንዲሶቹ እነዚህን ከአሰሳ ኮምፒውተሮች ጋር ለማገናኘት በቅተዋል። ኦዲሴየስ ማረፍ ብትችልም መጀመሪያ ላይ ምንም መልዕክት አልነበራትም። ደቂቃዎች እያለፉ ሲሄዱ ብዙዎች ድንጋጤ ውስጥ ገብተው የነበረ ቢሆንም ደቂቃዎች ሲያልፉ ደካማ ቢሆንም የግንኙነት ትስስር ተፈጠረ። ይህም የመቆሚያ እግሮቿን በተመለከተ አንዳንድ ስጋቶች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል። በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ግን ኦዲሴየስ ቀጥ ብላ ቆማ ምስሎችን ጨምሮ መረጃዎችን እየላከች መሆኑን ኢንትዩቲቭ ማሽንስ ገልጿል።
የታለመው የማረፊያ ቦታ ማላፐርት ተብሎ ከሚጠራው 5 ኪሎ ሜትር ከፍታ ካለው የተራራ አጠገብ ያለ የተሰነጠቀ መሬት ነበር። ይህም ናሳ በመጪዎቹ አስርት ዓመታት የጠፈር ተጓዦችን ለመላክ ካሰበባቸው ዕጩ ቦታዎች ውስጥ ይገኝበታል። በዚህ ክልል ውስጥ በቋሚነት በጥላ ውስጥ በመሆናቸው ምንም ዓይነት የፀሐይ ብርሃን የማያገኙ ጥልቅ ጉድጓዶች አሉ። ሳይንቲስቶች በረዶ የሠራ ውሃ በውስጣቸው ሊኖር ይችላል ብለው ያስባሉ። የናሳ የፕላኔቶች ሳይንስ ዳይሬክተር የሆኑት ሎሪ ግላዝ "በረዶው በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም በጨረቃ ላይ ያለውን በረዶ መጠቀም ከቻልን ከኛ ጋር ማምጣት ያሉብን ቁሳቁሶች አነስተኛ ይሆናሉ" ብለዋል። "ይህን በረዶ ወደ መጠጥ ውሃ በመቀየር ልንጠቀምበት እንችላለን። ለነዳጅ ሃይድሮጂንን እና የጠፈር ተመራማሪዎች የሚተነፍሱትን ኦክስጅን ልናወጣለት እንችላለን። ስለዚህ በሰው ልጅ ፍለጋ ውስጥ ይረዳናል" ብለዋል።
በኦዲሲየስ ቦርድ ላይ የተጫኑት የናሳ ስድስት መሣሪያዎች የቴክኖሎጂ ማሳያ እና ሳይንስ ነው። ዋናው ምርመራ የአፖሎ ጠፈርተኞች ከባድ ችግር ሆኖ ያገኙትን የጨረቃ ብናኝ ባህሪ መመልከት ነው። የኤጀንሲው ሳይንቲስቶች አቧራው እንዴት እንደሚነሳ በደንብ ለመረዳት ይፈልጋሉ። የኤምብሪ-ሪድል ኤሮኖቲካል ዩኒቨርሲቲ የተማሪ ካሜራም በሮቦቱ ላይ ተገጥሟል። ይህ ካሜራ የተዘጋጀው ሮቦቱ ሲያርፍ ራሱን ፎቶ ለማንሳት ነው። አሜሪካዊው ሰዓሊ ጄፍ ኩንስ ጨረቃ በወር ውስጥ ያላትን የተለያዩ ደረጃዎችን የሚወክሉ 125 ትንንሽ እና ከማይዝግ ብረት የተሠሩ ኳሶችን የያዘ ሳጥን ከሮቦቱ ጎን አያይዟል።
Comments
Post a Comment