ሥራችንን በሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ልንነጠቅ እንችላለን?

የቴክኖሎጂ እያደር መምጠቅ ዕድል ብቻ ሳይሆን ስጋትንም ይዞ መጥቷል። የሰው ሰራሽ አስተውሎት (የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ፣ ኤአይ) እድገት የዓለም ኃያላን መንግሥታትን ጭምር ስጋት ውስጥ ከትቷል። እንዴት ልንቆጣጠረው እንችላለን? ካልተቆጣጠርነው ምን ሊያስከትል ይችላል? ዓለምስ ወደፊት ምን መልክ ይኖራታል? የሚሉ ጥያቄዎች መነጋገሪያ ከሆኑም ሰነባብተዋል። በተለይ ባደጉት አገራት በሰው ሰራሽ አስተውሎት ምክንያት ሥራችንን ልናጣ እንችላለን በሚል በርካታ ሰዎች ካሁኑ ጭንቀት እየተዳረጉ ነው።

ክሌር ተቀማጭነቱን ለንደን ያደረገ አማካሪ ድርጅት ውስጥ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሆና ለስድስት ዓመታት ሰርታለች። የ34 ዓመቷ ክሌር ሥራዋን ትወዳለች። በምታገኘው ደመወዝም ቢሆን ደስተኛ ናት። ይሁን እንጂ ባለፉት ስድስት ወራት ሥራዬን ላጣ እችላለሁ የሚል ሥጋት አድሮባታል። ምክንያቱ ደግሞ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ነው። በእርግጥ ክሌር አሁን ላይ የምትሰራውን ሥራ ሙሉ በሙሉ ማሽን ይተካዋል ብላ አታስብም። ሆኖም የቅርብ የቴክኖሎጂ ክስተት የሆነው ቻትጂፒቲ (ChatGPT) ውስብስብ እየሆነ መምጣቱ ያስገርማታል። በዚህም ከተወሰነ ዓመታት በኋላ የምትሰራውን ሥራ ማሽን ሊያከናውነው እንደሚችል ትገምታለች። ይህ በሥራዋ ላይ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ማሰብ ደግሞ ያስጠላታል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሮቦቶች የሰዎችን ሥራ ሊነጥቁ እንደሚችሉ እና እንደ ቻትጂፒቲ ያሉ የሰው ሰራሽ አስተውሎት የቴክኖሎጂ ውጤቶች በፍጥነት ወደ ሥራ መግባታቸው አርዕሰተ ዜና ሆነዋል። አንዳንድ ሠራተኞችም ክህሎታቸው ወደፊት በሥራ ገበያው ላይ ምን ያህል ይፈለግ ይሆን? በሚል ስለወደፊታቸው መጨነቅ ጀምረዋል። በደኅንነት፣ በገንዘብ እና በአስተዳደር ላይ የሚሰራው ዓለም አቀፉ ተቋም ጎልድማን ሳክስ፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት 300 ሚሊዮን የሙሉ ሰዓት ሥራዎችን ሊተካ እንደሚችል የሚያሳይ አንድ ሪፖርት መጋቢት ላይ አውጥቶ ነበር።

ባለፈው ዓመት የወጣው የፒደብሊውሲ (PwC) ዓመታዊ ዓለም አቀፍ የሠራተኛ ኃይል ዳሰሳ ጥናት እንዳሳየውም፣ በጥናቱ ከተሳተፉት ውስጥ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት መላሾች በሦስት ዓመታት ውስጥ ሚናቸው በቴክኖሎጂ ይተካል በሚል ተጨንቀዋል። በዩናይትድ ኪንግደም ብሪስቶል የምትኖረው የ29 ዓመቷ ፀሐፊ አሊይስ ማርሻል፣ “ሥራችንን በቴክኖሎጂ ልንነጠቅ እንችላለን” በሚል በርካታ የፈጠራ ባለሙያዎች እንደሰጉ አስባለሁ” ትላለች። ይሁን እንጂ ደንበኞቻቸው የእነርሱን ዋጋ እንደሚገነዘቡ እና ከሰው ሰራሽ አስተውሎት መሣሪያዎች ዋጋ እና ምቾት ይልቅ የሰውን ትክክለኛነት እንደሚመርጡ ተስፋ እንደምታደርግ ትናገራለች።

የሥራ አሰልጣኞች እና የሰው ኃይል አስተዳደር ባለሙያዎችም በሠራተኞች ዘንድ ጭንቀት ማየታቸውን ገልጸው፣ ተቀጣሪዎች መቆጣጠር በሚችሉት ነገር ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል። ሥራዬን በማሽን ምክንያት አጣለሁ በሚል ከመጨነቅ ፋንታም ከቴክኖሎጂ ጋር እንዴት መሥራት እንዳለባቸው ራሳቸውን ማስተማር ላይ ጊዜያቸውን እና አቅማቸውን ማዋል አለባቸው ሲሉም ይመክራሉ። ባለሙያዎቹ እንደሚሉት ሠራተኞች ቴክኖሎጂን እንደ ስጋት ሳይሆን እንደ ሐብት ከቆጠሩት ለሥራ ቀጣሪዎች ራሳቸውን ተፈላጊ በማድረግ ጭንቀታቸውን መቀነስ ይችላሉ።

'ህልም ተፈርቶ . . . '

ለአንዳንድ ሰዎች የሰው ሰራሽ አስተውሎት መሣሪያዎች በፍጥነት ዕውን እንደሆኑ ይሰማቸዋል። የኦፕንኤአይ ፈጠራ የሆነው ቻትጂፒቲ ባንድ ሌሊት የተፈጠረ ነው የሚመስለው። የሰው ሰራሽ አስተውሎት መሣሪያ ውድድርም በየቀኑ እየጨመረ መጥቷል። ይህም ሠራተኞች በሥራቸው ላይ ስለመቆየታቸው እርግጠኝነትን አሳጥቷል። በኒው ዮርክ የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የሥራ አሰልጣኝ እና መምህር የሆኑት ካሮላይን ሞንትሮስ፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ለውጦች እና የሚሰሩበት ፍጥነት አስፈሪ ሊሆን እንደሚችል ይስማማሉ። የሰው ሰራሽ አስተውሎት እድገቱ ፈጣን በመሆኑ እና ያልታወቁ በርካታ ተፅዕኖዎችን ሊያስከትል በመቻሉ፣ በዚህ ላይ መጨነቁ አዲስ አይደለም ይላሉ ሞንትሮስ። በመሆኑም ሠራተኞች በዚህ ሊጨነቁ እንደማይገባ፣ ይልቁንም ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም ራሳቸውን ማብቃትን ምርጫቸው ማድረግ እንዳለባቸው ይመክራሉ።

የቴክኖሎጂ ፈጠራ ማዕከል የሆነው ላይከንስም ተመሳሳይ ሃሳብ ነው ያለው። “ቴክኖሎጂ እድገት አሳይቷል። ቴክኖሎጂ የሥራ ሒደቶችን የማቀላጠፍ አቅም አለው። በመሆኑም ሰዎች ከእነዚህ የቴክኖሎጂ እድገቶች ጋር ራሳቸውን ማስማማት አለባቸው” ብሏል። ተቋሙ እንደሚለው ከሠው ሰራሽ አስተውሎት ፈጣን እድገት ጋር በተያያዘ የሚከሰት ጭንቀትን ለመቀነስ ሠራተኞች ስለሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) እንዲማሩ እና አዳዲስ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ መርዳት ያስፈልጋል። “ሠራተኞች ከቴክኖሎጂ ለመራቅ ከማሰብ ይልቅ ለመቀራረብ እና ለመማር ማቀድ አለባቸውም” ብሏል። እንደ ላይከንስ ከሆነ እንዲህ ዓይነት ክስተት ሲያጋጥም ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ከዚህ ቀደምም በንግድ፣ በምርት እና በሌሎች ዘርፎች ላይ ተመሳሳይ የቴክኖሎጂ መገዳደር ገጥሟል። በዚህም የአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መፈጠር የተወሰኑ ሰዎችን የማያስደነግጥ ሆኖ ቆይቷል ይላል። ሞንትሮስም ካለፉት አዳዲስ የቴክኖሎጂ እድገቶች ብዙ መልካም ነገሮች እንደመጡ እና ለውጡ ለማኅበረሰብ እድገት ቁልፍ ግብዓት ሆኖ መቆየቱን ይናገራሉ። “ሰዎች ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ምንም ዓይነት ምላሽ ቢሰጡም፣ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው። በመሆኑም ሰዎች ክህሎታቸውን ለማሻሻል እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ የሚጨነቁ ከሆነ ይህ ከቴክኖሎጂው በበለጠ ይጎዳቸዋል” ሲሉም ሞንትሮስ ይመክራሉ።

የሰዎች የተለየ ዋጋ

ባለሙያዎች እንደሚሉት ሰዎች በሰው ሰራሽ አስተውሎት ምክንያት ሥራቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ በመስጋት በተወሰነ ደረጃ ጭንቀት ቢታይም፣ ከቁጥጥር ውጪ በሆነ መንገድ ለመጨነቅ ግን ጊዜው አሁን ላይሆን ይችላል። በቅርቡ የወጡ የተወሰኑ ጥናቶች እንዳመለከቱት ሮቦቶች የሰዎችን ሥራ ሊተኩ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ።

በአሜሪካ ኡታህ ግዛት በሪንግሃም ያንግ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጥናት ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ኤሪክ ዳህሊን፣ እንደ አውሮፓውያኑ ኅዳር 2022 የሰሩት ጥናት እንደሚያመለክተው፣ ብዙ ሰዎች በሚያምኑት መጠን ሮቦቶች የሰውን አለመተካታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ሰዎች አውቶማቲክ መሣሪያዎችን እየተቆጣጠሩበት ያለውን መጠንም የሚረዱት በተሳሳተ መንገድ ነው። ጥናቱ እንደሚያሳየው 14 በመቶ ሠራተኞች ሥራቸው በሮቦቶች ሲተካ እንዳዩ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ በቴክኖሎጂ ምክንያት ሥራቸውን ያጡ ሰዎችም ሆኑ እየሆነ ያለውን አጋነው ያልተመለከቱ ሰዎች ግምት ከእውነታው የራቀ ነው። ዳህሊን “በአጠቃላይ ሮቦቶች ሥራችንን ሊወስዱት ይችላሉ የሚለው አረዳድ እጅጉን የተጋነነ ነው። ሥራቸውን ያላጡት ይህንን በእጥፍ ይገምታሉ። ሥራቸውን ያጡት ደግሞ በሦስት እጥፍ ይገምቱታል” ብለዋል።

ተመራማሪው እንደሚሉት የተወሰኑ ቴክኖሎጂዎች የሚያስከትሉት ነገር ከግምት ሳይገባ ተግባራዊ ሊደረጉ ይችላሉ። ሆኖም ቴክኖሎጂ በሆነ ዘርፍ ጥቅም ላይ ዋለ ማለት ይተገበራል ማለት አይደለም። በኢዋይ አማካሪ ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት ስቴፋኒ ኮልማን በበኩላቸው የወደፊቱ የሠራተኛ ኃይል አንድ ወጥ ይሆናል ብለን መጠበቅ የለብንም ይላሉ። የሰዎች እና የሮቦቶች ውህደት ሁልጊዜም ሊኖር ግድ ነው። “ሰዎች ሮቦቶች የማይሰሩትን ሥራ መሥራት አለባቸው። እንዲህ ዓይነቱ ሥራ የሰዎችን ተፈጥሯዊ ብቃት ይፈልጋሉ። ለምሳሌ የግንኙነት መፍጠር፣ ፈጠራ እና ስሜትን መቆጣጠርን (ኢሞሽናል ኢንተለጀንስ) መጥቀስ ይቻላል። በመሆኑም “በሠራተኛው ኃይል ላይ የሰዎችን ልዩ የሆነ ዋጋ ማወቅ በዚህ ርዕስ ዙሪያ ያሉ ስጋቶችን ለማወቅ ወሳኝ እርምጃ ነው” ብለዋል።

ምንጭ፦

BBC Amharic - https://www.bbc.com/amharic/articles/c4npvwjp7k0o

Comments