ሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ/ኤአይ) ዓለምን እያስደነቀ፣ እያሸበረም ይገኛል። የበርካቶች ስጋት በዚህ ቴክኖሎጂ ምክንያት የእንጀራ ገመዳችን ይበጠሳል የሚለው ነው። የጥናት ጽሑፍ የሚሠራው ኤአይ፣ የሚያክመው ኤአይ፣ ልጅ የሚያጫውተው ኤአይ፣ የሚያጸዳው ኤአይ፣ መንገድ የሚያመላክተው ኤአይ፣ የሚያስተምረው ኤአይ. . . ታዲያ ሰዎች ቦታቸው የቱ ጋር ነው? የሰውን ክህሎት በመቅዳት የተሠራው ኤአይ አንድ ቀን ፈጣሪዎቹ ሰዎችን ያስንቅ ይሆን? የማይካደው ነገር ኤአይ የሰው ልጅን በቅልጥፍና እየበለጠ መምጣቱ ነው። ተፈጥሯዊው እና መሠረታዊ የሰዎች ልህቀት ግን ቢያንስ ለጊዜው አይተኬ ነው። የቴክኖሎጂ ወደፊት መገስገስ ከአእምሯችን በላይ ሲሆን፣ በቀጣይ ስለሚመጣው የሥራ ዓለም መጨነቃችን አያስገርምም። ከዚህ አኳያ በየትኛው የሙያ ዘርፍ ብሰማራ ነው ዓለም ጥሎኝ የማይሄደው? ብሎ ማሰብም አይቀርም። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ይህ የቴክኖሎጂ ዘመን የሥራ በር ከፍቶላቸው ሀብት ያካበቱ ጥቂት አይደሉም። በዚህ ዘገባ ሰው ሰራሽ አስተውሎት/ኤአይ ከደቀናቸው ስጋቶች አሻግረን ዘመኑ የፈጠራቸውን የሥራ ዕድሎች እንቃኛለን። ኤአይ በቅርቡ የማይተካቸውን ዘርፎችም አያይዘን እናነሳለን።
ቴክኖሎጂ የትኞቹን ሥራዎች ፈጠረ?
ቴክኖሎጂ ያስቀራቸው፣ ያሻሻላቸው፣ ያጠፋቸው ሥራዎች እንዳሉ ሁሉ፣ እንደ አዲስ ዘርፍ ያመጣቸውስ?
የአይኮግ ላብስ ሥራ አስኪያጅ ጌትነት አሰፋን አስተያየቱን ጠይቀናል። ላለፉት አሥር ዓመታት በሰው ሠራሽ አስተውሎት እንዲሁም ተያያዥ የቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ የሠራ ተቋም መሥራች ነው። “ብዙዎች ቴክኖሎጂ ሥራን ሙሉ በሙሉ ያጠፋል ብለው ያስባሉ። በተወሰነ መንገድ ስናየው ልክ ናቸው። አሁን ሥራ ብለን የምጠራው ሥራ ለወደፊት አይኖርም” ይላል ባለሙያው። ይህ ማለት ሥራ በአጠቃላይ ይጠፋል ማለት ግን አይደለም። እንደማንኛውም ዘርፍ ሥራም ይለወጣል። ለምሳሌ ከዘመናት በፊት ጽሑፍ በበግ እና በፍየል ቆዳ ላይ ነበር የሚጻፈው። ተሻሽሎ በታይፕ ይተየብ ጀመር። መቶ ገጽ ቢፈለግ መቶ ጊዜ ይተየባል። ታይፕን ኮምፒውተር ተክቶታል። መቶ ጊዜ መተየብ ሳያስፈልግ አንድ ገጽ ኮፒ ይደረጋል። ፀሐፊ ሳያስፈልግ ቃላትን እየሰማ ወደ ጽሑፍ የሚለውጥ ማሽን መጥቷል።
ከጥቂት ወራት በፊት ጎልድማን ሳችስ ባወጣው ግምት ይዘት መፍጠር የሚችል ኤአይ አሁን ሰዎች የሚሠሩትን ሲሶውን መሥራት ይችላል። በአውሮፓ እና አሜሪካ ብቻ በሰዎች የሚሠራ ሥራን በማሽን በማሠራት (Automation) 300 ሚሊዮን ሥራዎች ይታጣሉ።
ቴክኖሎጂ ካመጣቸው ሥራዎች መካከል የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ (Social Media Influencer) ይጠቀሳል። ዓመታት ወደኋላ ተመልሰን አንድ ሰው “ሥራዬ የሰዎች አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ነው” ቢል ወይም ብትል ቀልድ ሊመስለን ይችላል። ራሳቸውን በልዩ መንገድ በማስተዋወቅ፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ተከታዮች በማፍራት፣ ለተከታዮቻቸው ማስታወቂያ በመሥራት ከማስታወቂያው በሚገኘው ገቢ ይተዳደራሉ። ሙያው ዛሬ ከፍተኛ ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት ነው።
ሥራ ይጠፋል?
ባለሙያው እንደሚለው፣ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ ምጣኔ ሀብት እስካልተፈጠረ ድረስ ሥራ አይጠፋም። “የነበሩ ሥራዎች ይሞታሉ። አዳዲስ ሥራዎች ደግሞ እየፈጠርን እንሄዳለን” ሲል ያስረዳል። በማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ተመርኩዞ መፍትሄ መስጠት አዳዲስ ሥራዎች የሚፈጠርበት አንዱ መንገድ ነው። ሌላው መንገድ አሁን ያሉ ሥራዎችን ከቴክኖሎጂ ጋር አጣምሮ ማዘመን ነው። ለምሳሌ ሕክምና በቴክኖሎጂ ታግዞ (Telemedicine) እየተተገበረ ይገኛል። ሐኪሞች ቤታቸው ሆነው በድረ ገጽ፣ በተለያዩ አገራት ሕክምና መስጠት ይችላሉ። አዳዲስ ነገሮችን መፍጠር እንዳለ ሆኖ ግብዐት እና የገንዘብ አቅም ውስን በሆነባቸው ሁኔታዎች ውስጥ ግን ፈጠራዎችን መቅዳት (Copying) የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ጌትነት ይመክራል። “ቻይና ለ40 ዓመታት ኮፒ ስታደርግ ነው የቆየችው። የዓለምን ሁለተኛውን ግዙፍ ምጣኔ ሀብት የፈጠሩት ኮፒ በማድረግ ነው” የሚለው የቴክኖሎጂ ባለሙያው፣ የአፍሪካ ወጣቶች ኢንተርኔት እና ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የራሳቸውን የሥራ ዓለም እንዲፈጥሩ ይመክራል። “የዕውቀት እና መረጃ እጥረት የለም። እንዴት ወደ ገንዘብ መለወጥ ይቻላል የሚለው ነው ጥያቄው” ይላል።
ኤአይ የማያጠፋቸው ሥራዎች አሉ?
ማርቲን ፎርድ ‘Rule of the Robots: How Artificial Intelligence Will Transform Everything’ የተባለ መጽሐፍ አላቸው። አሜሪካዊ የወደፊቱ ዓለም ተመራማሪ ናቸው። ከቢቢሲ ወርክላይፍ አምድ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኤአይ የማያጠፋቸው ሥራዎች አሉ? ተብለው ሲጠየቁ ሦስት ዘርፎችን ነው የጠቀሱት።
“ሦስት ዘርፎች ይቀራሉ ብዬ አምናለሁ። የመጀመሪያው የፈጠራ ዘርፍ ነው። ይሄ አንድን ነገር ከምንም የመፍጠር ዘርፍ ነው” ይላሉ። ሁሉም የፈጠራ ዘርፍ አይጠፋም ማለት ግን አይደለም። ለምሳሌ ግራፊክስ ዲዛይን እና ቪዥዋል ሥነ ጥበብ በዚህ አይካተቱም። ኤአይ የፈጠራ ውበትን ተረድቶ አዲስ ነገር እንዲፈጥር ማድረግ ቢቻልም፣ በሳይንስ፣ በሕክምና፣ በሕግ እና በንግድ ዘርፍ ያሉ አዳዲስ አመለካከቶችን መፍጠር የሚችሉት ሰዎች ናቸው።
“ሁለተኛው የማይጠፋው ዘርፍ ጥብቅ የሰው ለሰው ትስስር የሚጠይቅ ሥራ ነው” ይላሉ ማርቲን ፎርድ። ምሳሌ የሚሰጡት ነርሶችን፣ የንግድ አማካሪዎችን እና የምርመራ ጋዜጠኞችን ነው። እነዚህ ዘርፎች ሰዎችን በጥልቀት መረዳት የሚጠይቁ ናቸው። መግቢያችን ላይ እንደጠቀስነው ደግሞ ተፈጥሯዊው እና መሠረታዊ የሰዎች ልህቀት ግን ቢያንስ ለጊዜው አይተኬ ነው።
“ሦስተኛው ዘርፍ እንቅስቃሴ የሚጠይቁ ሥራዎች እና ችግር መፍታት የሚያስፈልጋቸው ሥራዎች ናቸው” ይላሉ ማርቲን ፎርድ። ቧምቧ ሠሪዎች እና ኤሌክትሪክ ጠጋኞች በዚህ ይካተታሉ። እነዚህ ሙያተኞች በየጊዜው የሚገጥሟቸው ችግሮች አዳዲስ ናቸው። ስለዚህ የማሰብ ችሎታቸውን ተጠቅመው መፍትሄ ማምጣት ይጠበቅባቸዋል። የሥራ ዘርፎች ባህሪያቸውን እየለወጡ እንደሚሄዱ ጌትነት ከማርቲን ፎርድ ጋር ይስማማል።
ባለሙያዎቹ የሚስማሙበት አንድ ነጥብ ኤአይ የሥራ ዓይነትን የሚለውጥ መሆኑ ነው። የሰው ለሰው ግንኙነት የሚያስፈልጓቸው ሙያዎች፣ የሰዎችን የማሰብ እና የማሰላሰል እንዲሁም የመወሰን ችሎታ የሚጠይቁ ሙያዎች እንዳሉ ይቀጥላሉ። አንድ ሰው ካንሰር እንዳለበት ለማወቅ በሚደረገው ምርመራ ኤአይ ከሰው በበለጠ ጥልቅ ጥናት አድርጎ የተሻለ መልስ ሊሰጥ ይችላል። ሰዎች ግን ሕክምናውን ማግኘት የሚፈልጉት ከሰው ነው። የሰዎችን ጉልበት የሚበዘብዙ ሥራዎች ወደ ማሽን ማሻገር ዘመኑ የደረሰበት ከፍታ ነው። በሌላ በኩል ኤአይን ጨምሮ ሌሎችም ፈጠራዎች አነስተኛ ገቢ የሚያገኙ የማኅበረሰብ አባላትን ወይም በፆታ እና በቀለም መገለል የሚደርስባቸውን የማኅበረሰብ ክፍሎች ባላማከለ መንገድ እንዳይቀረጹ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ምንጭ፦
BBC Amharic - https://www.bbc.com/amharic/articles/cy9075j8j24o
Comments
Post a Comment