ሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) የሰው ልጆች መጥፊያ ይሆናል?


ሰው ሠራሽ አስተውሎት ወይም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የሰው ልጆች ማብቂያ ይሆናል የሚለው ስጋት ከተሰማ ሰነባበተ። የኦፕንኤአይ እና ጉግል ዲፕማይንድ መሪዎች ማስጠንቀቂያውን ከሰጡት መካከል ናቸው። ለመሆኑ ማሽን እንዴት የሰዎችን ሕይወት ይቆጣጠራል? የሚለውን በዚህ ዘገባ እንቃኛለን። ሦስቱን የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ደረጃዎችን እንዳስሳለን። እነዚህ ‘አርቴፊሻል ናሮ ኢንተለጀንስ’፣ ‘አርቴፍሻል ጄኔራል ኢንተለጀንስ’፣ እና ‘አርቴፍሻል ሱፐር ኢንተለጀንስ’ ናቸው።

ቻትጂፒቲ በፍጥነት ኢንተርኔትን በመጠቀም በታሪክ ቀዳሚው ሆኗል። ሰው ሠራሽ አስተውሎት ተጠቅሞ ለጥያቄዎች መልስ የሚሰጥ መተግበሪያ ነው። ይህ ቴክኖሎጂ ለአገልግሎት በቀረበ በሁለት ወራት ብቻ 100 ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን አግኝቷል። ኢንስታግራም ይህን ያህል ተጠቃሚ ለማግኘት ሁለት ዓመት ተኩል ወስዶበታል። ቻትጂፒቲን የፈጠረው ኦፕንኤአይ ተቋም ነው። ማይክሮሶፍትም በገንዘብ አግዟል። ይህም የሰው ልጆች ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ላይ ጥያቄ እንዲነሳ ያደረገ ፈጠራ ሆኗል።

ለሰው ሠራሽ አስተውሎት ደኅንነት የሚሠራ አንድ ድርጅት “ለወረርሽኝ እና ለኒውክሌር ጦርነት የሚሰጠው ትኩረትን ያህል፣ በኤአይ ልንጠፋ እንችላለን የሚለውም የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ቀዳሚ አጀንዳ መሆን አለበት” ሲል ጽፏል። ሌሎች ባለሙያዎች ደግሞ ስጋቱ ተጋኗል ይላሉ።

ሰዎችን ማስመሰል

እንደ ቻትጂፒቲ፣ ዳል-ኢ፣ ባርድ እና አልፋኮድ ያሉ መተግበሪዎች ሐተታ፣ ግጥም፣ ቀልድ፣ ፎቶ፣ ሥነ ጥበብ እና ሌላም በሰው ልጆች የሚሠሩ ፈጠራዎችን ማምረት ጀምረዋል። ሰዎች ይሥሩት ማሽን፣ መለየትም አዳጋች ሆኗል። ተማሪዎች የቤት ሥራቸውን በማሽን ያሠራሉ። ፖለቲከኞች ንግግራቸውን በማሽን ያጽፋሉ። አይቢኤም 7,800 የሥራ ድርሻዎችን በኤአይ ስለሚሞላ ሰዎች እንደማይቀጥር ገልጿል። እነዚህ የሰው ሠራሽ አስተውሎት መነሻ ናቸው። የበለጠ እየጎለበተ እና እየዳበረ ሲሄድ ደግሞ የሰው ልጆች መጥፊያ ሊሆን ይችላል ብለው ባለሙያዎች ይሰጋሉ።

‘አርቴፊሻል ናሮ ኢንተለጀንስ’

ይህ አንድ ተግባር ላይ ያተኮረ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን የሚገልጽ ቃል ነው። አንድን ድርጊት ደጋግሞ የሚከውን ማሽን ማለት ነው። የሚማረው በስፋት ከሚሰበሰብ መረጃ ሲሆን፣ የሚሠራው ግን አንድ ድርጊት እንዲሆን ይደረጋል። ለምሳሌ ቼዝ የሚጫወት መተግበሪያን እንውሰድ። ሌላ ሥራ ባይሠራም በቼዝ ውድድር ዋንጫ እስከማንሳት ይደርሳል። ተንቀሳቃሽ ስልኮቻችን እንዲህ ባሉ መተግበሪያዎች የተሞሉ ናቸው። የበይነ መረብ ካርታ እና ሙዚቃ ማጫወቻን መጥቀስ እንችላለን። በዚህ ዘርፍ ያለ አሽከርካሪ የሚጓዙ መኪኖች እና ቻትጂፒቲም ይካተታል። ከአንድ ድርጊት በላይ መፈጸም ስለማይችሉ በራሳቸው ውሳኔ አያሳልፉም። ራሳቸውን በራሳቸው ማስተማር ግን ይቻላቸዋል።

‘አርቴፊሻል ጄኔራል ኢንተለጀንስ’

ይህ ማሽን ልክ እንደ ሰው ልጆች የአእምሮ ብቃት የሚጠይቅ ሥራን ሲከውን የምንደርስበት ይሆናል። ‘ጠንካራው ኤአይ’ የሚባለውም ለዚህ ነው። ከወር በፊት ከአንድ ሺህ በላይ የቴክኖሎጂ ሙያተኞች “ሁሉም የኤአይ ቤተ ሙከራዎች ቢያንስ ለስድስት ወራት ከቻትጂፒቲ-4 በላይ የሚደርስ ማሽንን ማሠልጠን እንዲያቆሙ” ጠይቀዋል።

የአፕል አጋር መሥራች ስቲቭ ዋዝኒክ “ከሰው የአእምሮ ብቃት ጋር የሚገዳደሩ ሥርዓቶች ለማኅበረሰብ እና ለሰው ዘር ስጋት ናቸው” ብሏል። የቴስላ፣ ስፔስኤክስ እና የትዊተር ባለቤት ኤሎን መስክም ተመሳሳይ ሐሳብ ሰንዝሯል። ቻትጂፒቲን የፈጠረው ኦፕንኤአይ አጋር መሥራች የነበረ ቢሆንም ባለመስማማት ለቋል። ባለሙያዎቹ በጻፉት ደብዳቤ እንዳሉት ተቋማት ሥራቸውን ለመግታት ካልተስማሙ “ደኅንነትን ለማረጋገጥ መንግሥታት ጣልቃ መግባት አለባቸው።”

ደካማም ብልህም የሆነው ማሽን

በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የኤአይ ሥነ ምግባር ተቋም የምትሠራው ካሪሳ ቬልዝ ደብዳቤውን ከፈረሙት አንዷ ናት። በእርግጥ “ኤአይ የሰው ልጆች መጥፊያ ይሆናል የሚለው ድምዳሜ የተጋነነ ነው” ትላለች። “አሁን እየሠራነው ያለው ኤአይ ደካማም ብልህም ነው። ቻትጂፒቲ እና ሌሎችም መተግበሪያዎች ትልልቅ ክፍተት አላቸው” ስትል ታስረዳለች። ሰው ሠራሽ አስተውሎት ሐሰተኛ መረጃ ሊያመነጭ ይችላል ብላ ትሰጋለች። “የአሜሪካ ምርጫ እየተቃረበ ነው። ትዊተር እና ሌሎችም ተቋማት የኤአይ ሥነ ምግባር ክፍላቸው ሠራተኞችን እያባረሩ ነው። ይህም ያስፈራል” ትላለች። የአሜሪካ መንግሥትም ስጋቱን ገልጿል።

“ኤአይ የዘመናችን ኃያል ቴክኖሎጂ ነው። ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድንሆን ችግሮቹን መቅረፍ አለብን” ሲል ዋይት ሐውስ መግለጫ አውጥቷል። የአሜሪካ ምክር ቤት የኦፕንኤአይ ዋና ኃላፊ የሆነውን ሳም አልትማን ስለ ቻትጂፒቲ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠርቶት ነበር። ኤአይ አቅሙ እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ መንግሥት ቁጥጥር ማድረግ እንዳለበት ምስክርነቱን ሰጥቷል። የሕዝብ ፖሊሲ አጥኚው ካርሎስ ኢግናሲዮ ጉቴሬዝ እንደሚለው፣ እንደ አየር ንብረት ለውጥ ኤአይን የሚቆጣጠር የባለሙያዎች ቡድን አለመኖሩ ያሳስባል።

‘አርቴፊሻል ሱፐር ኢንተለጀንስ’

ይሄ ሦስተኛው ደረጃ ነው። የመጨረሻውም ነው ይባላል። ኤአይ ከሰው ልጆች የላቀ ሲሆን፣ የሚደርስበት ደረጃ ይሆናል። የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ፈላስፋ እና የኤአይ ባለሙያ ኒክ ቦስቶርም እንደሚለው በዚህ ደረጃ “የሰው ልጆች ምርጥ አስተሳሰብ የደረሰበትን በልጦ ማሽን ይከውናል።” ይህም በሳይንስ፣ በፈጠራ፣ በማኅበራዊ እና ሌሎችም ዘርፎች ይስተዋላል። ሰዎች መሃንዲስ፣ ጠበቃ ወይም ነርስ ለመሆን ረዥም ጊዜ መማር ሊጠበቅባቸው ነው። በዚህ ደረጃ ከሰዎች በላቀ ማሽን ራሱን እያሻሻለ መሄዱ ያሰጋል።

ሳይንሳዊ ልቦለድ

ከአስርት ዓመታት በፊት በተሠራው ‘ተርሚኔተር’ ፊልም ላይ ማሽን ሰዎችን ለማጥፋት ጦርነት ሲያስነሳ ይታያል። በፕሪንስተን ዩኒቨርስቲ ኮምፒውተር ሳይንቲስት የሆነው ኧርቪንድ ናራያና እንዲህ ሳይንሳዊ ልቦለድ የሆነ ነገር ላይፈጠር ይችላል ይላል። “እንዲህ ያለ ተግባር ለመፈጸም የሚበቃ ኤአይ አይደለም አሁን እየሠራን ያለነው። እንዲህ ያሉ ፊልሞች ከእውነተኛው ስጋት ያዘናጋሉ” ሲል ያስረዳል። የሰው ልጆች ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ዕውቀት ማሽን ይተካል ወይስ አይተካም የሚለው አከራካሪ ነው። በተለይ ደግሞ ስሜት ላይ ያተኮረ የሰው ልጅ ብቃት በማሽን ይለወጣል? የሚለው ያጠያይቃል።

የኤአይ ‘አባት’ የሚባሉት ጄፍሪ ሂንተን ሰው ሠራሽ አስተውሎት መድረስ የሚችለው ጥግ እየተቃረበ ነው ብለው አሳስበዋል። “አሁን ማሽኖች ከእኛ የተሻለ አያስቡም። በቅርቡ ግን ይደርሱብናል ብዬ አስባለሁ” ብለዋል የቀድሞው የጉግል ሠራተኛ። ከሥራቸው የለቀቁት “ክፉዎች ኤአይን ለክፋት ያውሉታል” ብለው በመስጋታቸው እንደሆነም ሂንተብ አክለዋል። አሁን ባለው ሁኔታ ግን ኤአይ ሰዎችን የሚያግዝበት ደረጃ ላይ እንደሆነ አክለዋል።

የሰው ልጆች መጥፊያ?

እንግሊዛዊው የፊዚክስ ሊቅ ስቴቨን ሆኪንግ ቀድሞ ማስጠንቀቂያ የሰጠ ባለሙያ ነው። እአአ በ2014 “ሙሉ ሰው ሠራሽ አስተውሎት መሥራት የሰው ልጅ ማብቂያ ይሆናል” ብሎ ነበር። በዚህ ደረጃ የሚሠራ ማሽን በራሱ እንደሚመራ እና ራሱን እንደሚያሻሽልም ተናግሯል።

የኤአይ ተስፋ ከሚታያቸው አንዱ የሆነው ሬይ ኩርዝዊል ነው። በጉግል የኤአይ ተመራማሪው እና የቫሊ ሲንጉላሪቲ ዩኒቨርስቲ አጋር መሥራቹ ሬይ፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ሰዎች በተፈጥሯቸው ያሉባቸውን ውስንነቶች እንደሚሞላ ያምናል። በ2030 በናኖቦትስ አማካይነት የሰው ልጆች ሞትን ማስወገድ ይቻላል ብሎ ይተነብያል። ናኖቦትስ እጅግ ጥቃቅን እና በሰውነታችን ውስጥ ሕመምን የሚያክሙ ሮቦቶች ናቸው።

ኤአይን መቆጣጠር

ባለሙያዎች ሰው ሠራሽ አስተውሎትን ወይም አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤአይ) መቆጣጠር የሚቻልበት ሥርዓት መዘርጋት እንዳለበት ያሳስባሉ። “አንድ ማሽን በምድር ያሉ ሰዎችን መረጃ በሙሉ ሲያውቅ አስቡት እስኪ። ማሰብ ከምንችለው በላይ ነው የሚቆጣጠረን” ይላል ከባለሙያዎቹ አንዱ። ስጋቱ ሰዎች ከሮቦቶች ጋር ጦርነት ይገጥማሉ አይደለም። ከሰው ልጆች የበለጠ ማገናዘብ የሚችል ማሽን ተፈጥሮ፣ ሰዎች በማሽኑ ቁጥጥር ሥር መሆናቸውን ሳያውቁ ሕይወታቸው በማሽን እየተዘወረ ሲቀጥል ማየት ነው የሚያስፈራው።

ምንጭ፦

BBC Amharic - https://www.bbc.com/amharic/articles/c045z031j88o

Comments