የቻይናው የመንግስት ጋዜጣ ፒፕልስ ዴይሊ ሮቦት ዜና አንባቢ ስራ ማስጀመሩ ተነግሯል። በቀን 24 ስአት አመቱን ሙሉ ሳታርፍ መስራት ትችላለች የተባለችው ሮቦት “ሬን ሺያሮንግ” የሚል ስም ተሰጥቷታል። በሰው ሰራሽ አስተውሎት የበለጸገችው ዜና አንባቢ የኦንላይን የጋዜጣው አንባቢዎች ለሚያነሷቸው የተለያዩ ጥያቄዎችም ምላሽ ትሰጣለች ነው የተባለው።
“በሺዎች የሚቆጠሩ ዜና አንባቢዎች(ሰዎች) እውቀት አለኝ” የምትለው ሬን፥ “አስተያየታችሁ ይበልጥ ጎበዝ ያደርገኛል” በማለት ንግግሯንም ትቀጥላለች። ሮቦቷ ዜና አንባቢ በቻይና አንድ ቀበቶ አንድ መንገድ ፕሮጀክት፣ በቴክኖሎጂ እና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ጥልቅ እውቀት አላት መባሉን ዲይሊሜል አስነብቧል።
ቻይና ሰው ሰራሽ አስተውሎት ወይም አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሚጠቀሙ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ስራ ላይ እያዋለች ነው። ሽንዋ የተባለው የቻይና ዜና አገልግሎትም ሶስት (ሁለት ወንድ እና አንድ ሴት) ሪፖርተሮችን ወደ ስራ ማስገባቱ ይታወሳል። “ጂያንግ ላይላይ” የተባለች የመዝናኛ ፕሮግራም አቅራቢ ሮቦትም በ2019 በቴሌቪዥን መስኮት መታየቷ አይዘነጋም።
የአሜሪካው ፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ ያወጣው ጥናት እንደሚያሳየው በሮቦቶች ስራቸውን ከሚነጠቁ 20 የስራ አይነቶች ውስጥ ዜና አንባቢዎች ተካተዋል። የስልክ ጥሪ ማዕከል ሰራተኞች ቀዳሚዎቹ በሮቦቶች ስራቸውን ይነጠቃሉ የተባሉ ሲሆን፥ የቋንቋ፣ ህግ፣ ታሪክ እና እምነት አስተማሪዎች ደግሞ ተከታዩን ስፍራ ይይዛሉ። ሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚያሳድረው ተጽዕኖ በቀላሉ የሚገለጽ አለመሆኑንም ነው ተመራማሪዎች ያነሱት። ሮቦቶች የሰዎችን ስራ ከመረከባቸው ባሻገር ግን በጋራ በመስራት ስራ የሚያቀሉበት እድልም ሰፊ መሆኑ ተገልጿል።
ምንጭ፦
አል ዐይኒ - https://am.al-ain.com/article/meet-china-ai-news-anchor
Comments
Post a Comment